ዛሬ፡መስከረም18: ቀን (28 Sept 2018)

✞ በዓለ መስቀልን ምክንያት በማድረግ ከብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ✞

በመጀመሪያ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ፥ አደረሰን! ለዛሬ ንዑድ ክቡር ከሚኾን ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ያደረግሁትን [ምናባዊ] ቃለ መጠይቅ እጋብዛችኋለሁ፤ መልካም ቆይታ!

#ጥያቄ፡- አባታችን በመጀመሪያ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለልጆችህ ምዕዳን ለመስጠትና ለምንጠይቅህ አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ትሰጠን ዘንድ ፈቃድህ ስለ ኾነ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፤ ቡራኬህም ይድረሰን!

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ ይቀድሳችሁም፡፡ እናንተም ትጠይቁኝ ዘንድ ስለ ጠራችሁኝና ከእናንተ ጋር በዓሉን በማክበሬ ደስተኛ ነኝ፡፡

#ጥያቄ፡- መልካም አበታችን! እስኪ መጀመሪያ ስለ ራስህ ጥቂት ነገር ንገረን!

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- ስለ ራስ መናገር በክርስትና ደግ ባይኾንም እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ትመስሉ ዘንድ እነግራችሁ ዘንድ ግድ ኾነብኝ፡፡ አይሁዳዊ ስሜ “ሳውል” ይባል ነበር፡፡ ሳኦል ከሚለው ጋር በትርጉም አንድ ሲኾን “ከእግዚአብሔር የተለመነ” ማለት ነው፡፡ ከፈሪሳውያን ወገን የኾኑ ወላጆቼ ያወጡልኝ ስም ነው፡፡ ዕብራውያንና ከብንያም ነገድ የኾኑ አያቶቼና ቅድመ አያቶቼ ትውልዳቸው ገሊላ ነው፡፡ ወላጆቼ ግን የተመቸ ኑሮ ሲፈልጉ ከገሊላ ወደ ኪልቅያ ሔዱ፡፡ እኔም የተወለደሁት በንግዷ በታወቀችና የኪልቂያ ዋና ከተማ በምትኾን በጠርሴስ ነው። ሮማውያን በሥራቸው ለሚተዳደሩት ሕዝቦች ሮማዊ ዜግነትን ይሰጡ ስለ ነበር፥ አባቴም በዜግነት ሮማዊ ነበር። ይህም ለእኔ ተላልፎልኛል (ሐዋ.፳፪፡፳፬)። በተጨማሪም የዕብራስጥ ቋንቋ፣ የግሪክና የሮም የሌሎችንም በጠርሴስ ከተማ የሚኖሩትን ልዩ ልዩ አሕዛብን ቋንቋና የድንኳን ስፌት እየተማርኩ አደግኩ፡፡ ይህን እንግዲህ የምነግራችሁ በሮማዊነቴ ወይም ብዙ ቋንቋ መናገር በመቻሌ እንደ ቁም ነገር የምመካበት ነገር ኾኖ ሳይኾን ሳድግና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በማያልቀው ቸርነቱ ለሐዋርያነት በመረጠኝ ጊዜ አሕዛብን ለማስተማር ስለ ረዳኝ ነው፡፡

እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ዕድሜዬ እየተማርኩ ያደግሁት ከላይ የነገርኩአችሁንና መንፈሳዊ ትምህርትን ከፈሪሳዊው አባቴ ነው፡፡ ዕድሜዬ ፲፭ ዓመት ሲኾን ግን በአባቴ ፈቃድ ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ ከየኔታ ገማልያል የአይሁድን ሕግና ሥርዓት እንደዚሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ተጓዳኝ ነገሮችን ለ፲፭ ዓመታት ያህል ተማርኩ፡፡ የኔታ ገማልያል ፈሪሳዊ ስለ ነበር እኔም ይህን ፈሪሳዊነት ተቀብዬው ነበር። በ፴ ዓመቴም የአይሁድ ሸንጎ አካል ኾኜ ተቆጠርኩ። እንዲያውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን እኔ በኢየሩሳሌም ስለ ነበርኩ ኹኔታዎቹን ኹሉ ዐውቅ ነበር። እንዲህ በአይሁድ ሸንጎ አባልነት ለ፪ ዓመታት በምሠራበት ወቅትም ለኦሪታዊ እምነቴ እጅግ ቀናተኛ ነበርኩ፡፡ ከራሴ ሃይማኖትና ሕግ በቀር ሌላ ሃይማኖትና ሕግ ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡ የሌላውን ሃይማኖትና ሕግ እጅግ እነቅፍና እሳደብ ነበር፡፡ ስለ ሃይማኖት ብዬ ሌላውን ሰው ብገድል፣ ባጠፋም የጽድቅ ሥራ ይመስለኝ ነበር፡፡

#ጥያቄ፡- ግሩም ነው፡፡ እንግዲህ ደቀ መዝሙርህ የሚኾን ሉቃስ እንደ ነገረን በአስደናቂ መንገድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠራህ፡፡ አንተም ከሥጋዊና ከደማዊ ሰው ጋር ሳትማከር ተቀብለህ ወደ ክርስትናው መጣህ፡፡ ወደ ገዳም ሔደህ ለሦስት ዓመታት ከቆየህ በኋላም ተመልሰህ ወዲያው ሐዋርያዊ አገልግሎትህን አልጀመርክም ነበር – ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ሳታስተምር ቆይተሃል፡፡ እንግዲህ ከተጠራህበት ጊዜ ጀምረን ስንቈጥረው ዐሥራ ኹለት ዓመታት ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል ጊዜ ስትጠብቅ አይጨንቅም? ኃይልህንና ጉልበትህን ከጨረስህ በኋላ ወደ አገልግሎት መግባት አይከብድም? እንዴትስ ተስፋ አልቈረጥህም? እስኪ አጫውተን!

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- አዎ! በሥጋዊና በደማዊ ሰው እይታ ይህ የሚጨንቅ፣ የሚከብድና ተስፋ የሚያስቈርጥ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን የክርስትና ምሥጢሩ ያለው እዚህ ላይ ስለ ኾነ አይጨንቅም፤ አይከብድምም፡፡ እርግጥ ነው፡- “እንዴት ይኼን ያህል ዘመን ሳላገለግል? መምህረ አሕዛብ ትኾናለህ አላለኝምን? ታዲያ የታለ? አሁን በወጣትነቴ ካልሮጥኩ በሽምግልናዬ ወራት እንዴት ይቻለኛል?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ የእኔ ሥራ ግን ይህን መጠየቅ አልነበረም፡፡ የእኔ ሥራ እስከ ጊዜው ጊዜ መጠበቅ ነበር፡፡ ይህም ትርጕም የሚሰጠው፣ ስሜት የሚሰጠው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሥጋዊ ሰው አይደለም፡፡ እንዲያውም አንብባችሁ ከኾነ እንደዚያ በምጠብቅበት ጊዜ ላይ፡- “አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ፤ ታነጹም” ይላል ልጄ ሉቃስ (ሐዋ.9፡31)፡፡ ይህ ለምን ኾነ ያላችሁ እንደ ኾነ እግዚአብሔር እኛ ብቻ ተቈርቋሪ እንደ ኾንን እንድናስብ ስለማይፈልግ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ቤተ ክርስቲያን በእኛ ሳይኾን እኛ በቤተ ክርስቲያን ጥገኛ እንድንኾን ነውና!

#ጥያቄ፡- እንግዲህ ከዚህ ኹሉ በኋላ ነበር መደበኛ አገልግሎትህን የጀመርከው፡፡ እጅግ ስኬታማም ኾነሃል፡፡ እስኪ የዚህ ምሥጢሩ ምን እንደ ኾነ ደግሞ አጫውተን፡፡

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- ክርስትናን ደስታ አይደለም፡፡ እንዲሁ በፈንጠዚያ መኖርም አይደለም፡፡ ይህንም ከእኔ በደንብ መማር ትችሉ ዘንድ ጥቂት ጨምሬ ልንገራችሁ፡፡

ኹሉም ባይኾንም መከራ የክርስትና አንዱ ጌጥ ነው፡፡ ይህም ሌሎችን ማጽናናት እንድንችል – ለምሳሌ ታምመን የታመመን ማጽናናት እንድንችል ሊሰጠን ይችላል (2ኛ ቆሮ.1፡3-4)፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ይህ መከራ ተስፋ እስክንቈርጥ የሚያደርስ መከራ ሊኾን ይችላል (2ኛ ቆሮ.1፡8-9)፡፡ እኔም በዚህ ኹሉ አገልግሎቴ መካከል መከራ፣ ችግር፣ ጭንቀት፣ መገረፍ፣ ወኅኒ፣ ጦም፣ ሁከት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ መደብደብ፣ ፍርሐት፣ ግርፋት፣ ረሃብ፣ ራቁትነት ደርሶብኛል (2ኛ ቆሮ.11፡23-27)፡፡ ለምን ያላችሁ እንደ ኾነ ምሥጢሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡- “የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በእኔ ይገለጥ ዘንድ” (2ኛ ቆሮ.4፡8)፡፡

#ጥያቄ፡- ይኼ ኹሉ ሲደርስብህ ምንድን ነበር የምትለው?

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- “ትምክሕት የሚያስፈልግ ከኾነ ከድካሜ በሚኾነው ነገር እመካለሁ” (2ኛ ቆሮ.11፡30)፡፡

#ጥያቄ፡- ምን? ሰው እንዴት በችግር ይመካል? እንዴት በመገረፍና በእስራት ይመካል? እንዴት እንቅልፍ በማጣትና በመደብደብ ይመካል? እንዴት ሰው በፍሐት፣ በርሃብና በሚደርስበት ጭንቀት ይመካል?

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- በምነግራችሁ ነገር አትደንግጡ ልጆቼ! ኹሉንም አንድ በአንድ አስረዳችኋለሁ፡፡ የምነግራችሁ ነገርም በእኔ በአባታችሁ የደረሰ ብቻ እንጂ መጽሐፍ ጠቅሼ አይደለም የምነግራችሁ፡፡ ስለዚህ የዚህ ምሥጢሩ ምን እንደ ኾነ እነግራችኋለሁና ልቡናችሁን ሰጥታችሁ አድምጡኝ፡፡

ከዕለታት በአንዲቱ ቀን እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጥቄ ራእይ ተመለከትሁ፡፡ ሰው ሊሰማው የማይገባው ነገር ሰማሁ፡፡ ሰው ሊያየው የማይገባው ነገር አየሁ፡፡ ታዲያ ይህን ራእይ በማየቴ ልታበይ እንደምችል የሚያውቅ አምላኬ ጎኔን የሚወጋ ቀጭን ሰጥር ውጋት፣ ራሴን የሚቀጠቅጠኝ ፍልጠት ሰጠን፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር ያርቅልኝ ዘንድ ስለዚህ ቀኖና ገብቼ ሦስት ጊዜ ማልጀው ነበር፡፡ እርሱ ግን አይኾንም አለኝ፡፡ ለምን ስለው “ጸጋዬ ይበቃሃል” አለኝ፡፡

ይህን ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ በመሰደብ፣ በጸዋትወ መከራ፣ አገር ጥሎ በመሰደድ፣ ስለ ክርስቶስ ብሎ መራብና መጠማት፣ ይህም በመሰለ መከራ ኹሉ መመካት ወደድሁ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፡- “ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ” አልሁ (ገላ.6፡14)፡፡ ሰው ደካማ ሲኾን ይጮኻል፤ ሲጮኽ ጸጋ ያገኛል፡፡ ጸጋ ሲያገኝ ኃይለኛ ይኾናል፡፡ ስለዚህ “ችግር” ሲገጥማችሁ “ለምን?” ብላችሁ አታማርሩ፡፡ እኔ እንዳልኩት፡- “ጌታ ሆይ! ምን አደርግ ዘንድ ተወዳለህ?” በሉ እንጂ (ሐዋ.9፡6)፡፡

#ጥያቄ፡- አባታችን አንተ አሁን እንደ ነገርኸን ከኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከአንተ አርቀሃል፡፡ እኛስ ወደዚህ ደረጃ እንድንመጣ ምን እናድርግ?

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- አዎ! የመስቀል በዓልም አይደል?! የምትመኩበትን ነገር ዛሬ ምረጡ! የምትመኩበት ነገር የዘለዓለም ሕይወት የሚሰጣችሁ መኾኑን ርግጠኛ ኹኑ፡፡ ይህን ሕይወት የሚሰጣችሁም እኔ እንደ ነገርኳችሁ፥ ጌታችንም እንዳለ መከራ መስቀልን ስትሸከሙ እንጂ በገዛ ወንድማችሁ ላይ መከራ ስታደርሱ አይደለም፡፡ የዲያብሎስ መልእክተኛ የኾኑ አልያም ደግሞ አላዋቂ የኾኑ ሰዎች ከዚህ የሕይወት መርሕ ያወጡአችሁ ዘንድ ልክ ጌታችንን፡- “ከመስቀሉ ውረድና እንመንብህ፤ ራስህንም አድን” እንዳሉት ውረዱ ሊሉአችሁ ይችላሉ፡፡ ኾኖም ጌታችን አልወረደም፤ እናንተም ከዚያ አትውረዱ፡፡ ጌታችን ከመስቀል ቢወርድ ኖሮ አንድንም፤ እናንተም ከዚያ መስቀል ስትወርዱ የራሳችሁን መዳን አትፈጽሙም፡፡ በዚያ ስትጸኑ፣ በዚያ ስትተጉ ግን ከጌታችን መስቀል አጠገብ እመብርሃን እንደ ነበረች፥ ዛሬም እናንተን ለመርዳት ከመስቀላችሁ አጠገብ ትቆማለች (ዮሐ.19፡26)፡፡

ይህን ኹሉ ስታደርጉም ሰዎች ሊሳለቁባችሁ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ይህ በሥጋውያንና ደማውያን ሰዎች ዘንድ ሞኝነት ነው፡፡ በድካም መመካት ሞኝነት ነው፤ በፍርሐት መመካት ሞኝነት ነው፤ በጭንቀት መመካት ሞኝነት ነው፡፡ ለእናንተ ለምትድኑ ግን ይህ የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ ለእናንተ የዘለዓለም ሕይወት ለምታገኙ ግን ይህ ድካም፣ ይህ ጭንቀት፣ ይህ መከራ የእግዚአብሔር ኃይል የሚገለጥበት ነው፡፡

በልብ መታሰቡ፣ ቃል መነገሩ፣ በቅዱሳት መጻሕፍትም መነገሩ ከፍ ከፍ ይበልና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጥልን የገደለው በዚሁ በመከራ መስቀል ነው፡፡ አሁን በእናንተ ዘንድ እንደሚታየው ሰውን በመስቀል አይደለም፡፡ ሰውን መስቀል፣ ሰውን በቋንቋው ምክንያት ማሳደድ መሞት እንደ ኾነ ብታውቁስ ባልሰቀላችሁ፣ ባላሳደዳችሁም ነበር፡፡

# ጥያቄ፡- አባታችን ይህን ደኅና አድርገህ ብትነግረን!

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- ደስ ይለኛል፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይለኛል፡፡ ወንድሞች ሆይ! እኔን የምትመስሉ ኹኑ፤ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንኾንላችሁ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ፡፡ ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ኾነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፤ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ አሳባቸው ምድራዊ ነው፤ እኛ አገራችን በሰማይ ነውና (ፊልጵ.3፡17-20)፡፡ ለክርስቶስ መከራ መስቀል ጠላቶች ኾነው ይመላለሳሉና ማለቴም መከራ ማድረስን እንጂ ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን አይወዱም ማለቴ ነው፡፡ በዚህ ምድራዊ ጎሳቸው እንጂ በእግዚአብሔር አይመኩም ማለቴ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቢመኩ’ማ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን ሰው ከአገራችን ውጣ ባላሉት ነበር፡፡ በርግጥ ከአገራችን ውጣ ማለታቸው አገራቸው በሰማይ ሳይኾን በምድር መኾኑንና እነርሱም ገና ምድራውያን መኾናቸውን የሚያስታውቅ ነው፡፡ በኦሮሞነታቸው፣ በትግሬነታቸው፣ በአማራነታቸው፣ በሲዳማነታቸው፣ በወላይታነታቸው የሚመኩትን ያህል በእግዚአብሔር አይመኩም፤ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም አይመኩም፡፡ እንመካለን ቢሉም እንኳን በግብዝነት ነው፡፡ በከንፈር ብቻ ነዋ፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመከራ መስቀሉ ሰውንና እግዚአብሔርን፣ ነፍስንና ሥጋን፣ ሰውንና መላእክትን፣ ሕዝብንና አሕዛብን አንድ አደረገ፡፡ በእኛ ላይ የማስታረቅ ቃል ስላኖረም ደቀ መዛሙርቱ የምንኾን እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ብዙዎችን አስታረቅን፡፡ እናንተ የኢትዮጵያ ሰዎች ግን አንድ የኾነውን ሕዝብ ትለያያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ እስራኤል የተወደደውን ሕዝብ ታጣላላችሁ፡፡ ታዲያ ይህ ከውጭ ስትታዩ የክርስቶስ መስላችሁ ክርስቶስን የምታሳድዱ መኾናችሁ የሚያሳይ አይደለምን?

ዳግመኛም ጌታችን በመስቀሉ ፍቅርን አደረገ፡፡ ዕርቅን አወረደ፡፡ በቋንቋውና በጎሳው ምክንያት ወንድማችሁን የምታሳድዱ እናንተ ግን ጥልን ታደርጋላችሁ፡፡ ዕርቅን ትሽራላችሁ፡፡ መልሳችሁ ደግሞ “ከኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ” ትላላችሁ፡፡ ይህ በእውነት ያለ ሐሰት ግብዝነት ነው፡፡ ስለዚህ እኔን ምሰሉ!

#ጥያቄ፡- አባታችን ስላስተማርከን፤ ስለ ገሠጽከን እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡ በጸሎትህም አስበን!

#ቅዱስ #ጳውሎስ፡- አሜን አብሮ ያሰማን፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፥ ይቀድሳችሁም፡፡

Comments are closed.