ዛሬ፡መስከረም4፡ቀን (Sept 14 2018)

*እንኳን፡ከግብጽ፡ለኢትዮጵያ፡ሊቀ፡ጳጳስ፡ተሾመው፡ለመጡ፡በኢትዮጵያ፡ብዙ፡የዋሻ፡ቤተ፡ክርስቲያንን፡ላነጹ፡ለብጹዓዊ፡አቡነ፡ሙሴ፡ዘድባ፡የዕረፍት፡በዓል፣ለወንጌላዊው፡ቅዱስ፡ዮሐንስ፡የልደት፡በዓልና፡ለነዌ፡ልጅ፡ለቅዱስ፡ኢያሱ፡ለመታሰቢያ፡በዓሉ፡በሰላም፡አደረሰን።በተጨማሪ፡በዚች፡ቀን፡በስንክሳሩ፡ከሚታሰቡ፦ከእስክንድርያ፡ሊቀ፡ጳጳሳት፡ከአባ፡መቃርስ፡ዕረፍትና፡በአንጾኪያ፡በሰማዕትነት፡ከሞቱ፡ከ2መቶ፡ሰዎች፡ከመታሰቢያቸው፡ረድኤትና፡በረከትን፡ያሳትፈን።
*ብጹዕ፡አቡነ፡ሙሴ፡ዘድባ፦በአባታቸው፡የእቤታችን፡ጠባቂ፡የአረጋዊ፡ቅዱስ፡ዮሴፍ፡የልጅ፡ልጅ፡ሲሆኑ፤በእናቸው፡በኩል፡ድንግል፡ማርያም፡ከልጇ፡ጋር፡በቃና፡ዘገሊላ፡ሰርግ፡የተገኘችበት፡የዶኪማስ፡የልጅ፡ልጅ፡ናቸው።የአባታቸው፡ስም፡ቅዱስ፡ዮስጦስ፡ሲባል፤የእናታቸው፡ስም፡ቅድስት፡ጵስርስቅላ(ሶልያና፡ማርያም)ይባላል።

በሊቀ፡መላእክት፡ቅዱስ፡ገብርኤል፡አብሳሪነት፡ታህሣሥ8፡ተወለዱ።በዚህች፡ቀን፡ከእናታቸው፡እቅፍ፡በመውረድ፡ለአብ፡ለወልድ፡ለመንፈስ፡ቅዱስ፡ምስጋና፡ይሁን፤ከጨለማ፡ወደ፡ብርርሃን፡ላወጣኸኝ፡ብለው፡ፈጣርያቸውን፡አመስግነዋል።በ40ኛው፡ቀን፡የጌታ፡ሐዋርያት፡ጴጥሮስ፣ያዕቆብ፣ፊሊጶስና፡እንድርያስ፡ሆነው፡ጥር18፡ክርስትናን፡አቡነ፡ሙሴን፡አነሱዎቸው።በ3፡ዓመታቸው፡ወላጆቻቸው፡ለቤተ፡ከክርስቲያን፡ሰጧቸው።ቅዱስ፡ፋኑኤልና፡ቅዱስ፡ዮናኤል፡ሕብስት፡ሰማያዊ፡እያመጡ፡ይመግቧቸው፡ነበር።ከዚህ፡በኋላ፡መምህራቸው፡ዝክረ፡ጻድቅ፡ብሉያትንና፡ሐዲሳትን፡አስተማራቸው።በወንጌላዊው፡በቅዱስ፡ማርቆስ፡እጅ፡ዲቁና፡ተሾሙ።እመቤታችን፡ማርያምም፡ለብፁዓዊ፡ሙሴ፡ልፋፈ፡ጽድቅ፣ሰኔ፡ጎልጎታን፣ባርቶስና፡ራዕየ፡ማርያምን፡ሰታቸዋለች።ወገባቸውን፡ከጠጉር፡በተሰራ፡መታጠቂያ፡ይታጠቁ፡ነበር።አቡነ፡ዘበሰማያትም፡በጀመሩ፡ጊዜ፡ሰባቱ፡ሰማያት፡ተከፍተውላቸው፡ከአጋዕዝተ፡ዓለም፡ሥላሴ፡ጀምሮ፡ሁሉንም፡ቅዱሳን፡በግልጥ፡ያያሉ።ሲሰግዱ፡እንባቸው፡ደረታቸውና፡እግራቸውን፡እያራሰ፡በመሬት፡ይፈሳል።በዓለም፡ብዙ፡የዋሻ፡ቤተ፡ክርስቲን፡አንጸዋል።የሕንፃ፡ሥራ፡ከመደመራቸው፡በፊት፡40ቀን፡ይጾማሉ።ሁለቱ፡መላእክት፡ቅዱስ፡ፍርክኤልና፡ቅዱስ፡ፍናኤል፡እየረዷቸው፡መቅደስን፡ያንጻሉ።የዋሻ፡ቤተ፡መቅደስ፡ስራ፡ጎን፡ለጎን፡መስቀልና፡ሌሎች፡ንዋየ፡ቅዱሳት፡ይሰራሉ።የሚሰሯቸው፡መቅደሶች፡ከፊሉ፡የሚታዩ፡ምዕመናን፡የሚገለገሉባቸው፡ሲሆን፡የቀሩት፡የማይታዩ፡ስውራን፡የሚገለገሉበት፡ነው።

አቡነ፡ሙሴ፡ጵጵስና፡የተሾሙት፡በ12ቱ፡ሐዋርያት፡በአንድነት፡ነው።ዘመናቸውን፡ሁሉ፡ከ24ቱ፡ካህናተ፡ሰማይ፡ጋር፡በመሆን፡የአብ፡የወልድ፡የመንፈስ፡ቅዱስን፡መንበር፡አጥነዋል።በድንግልናቸው፡በንጽሕናቸው፡የከበሩ፡12ክንፍ፡የተጎናጸፉ፡ናቸው።ጥቂቶች፡ለማየት፡የታደሉትን፡ብሔረ፡ብፁዓን፡ሄደው፡አይተዋል

አቡነ፡ሙሴ፡በግብፅና፡በእስራኤል፡መካከል፡ሲካር፡በሚባል፡ቦታ፡ካገለገሉ፡በኋላ፡ጣዖታትን፡ለማሳፈር፡ወደ፡መቄዶንያ፡ሄደው፡ጣዖት፡አምላኪውን፡ንጉሥ፡ገሰጹት።ንጉሥ፡ተቆጥቶ፡አጥንታቸው፡እስኪሰበር፡ድረስ፡በብረት፡አስደብድቦ፡በብረት፡አልጋ፡ላይ፡አስተኝቶ፡እሳት፡አነደደባቸው።ቅዱስ፡ሚካኤልና፡ገብርኤል፡ግን፡ዳሰው፡ፈወሷቸው።በማግስቱ፡ወደ፡ፍርድ፡አደባባይ፡ቢወስዷቸው፡ምንም፡እንዳልሆኑ፡ንጉሡ፡በማየቱ፡በንዴት፡ሰውነታቸውን፡በሰይፍ፡አስቆራረጠ።ከሰውነታቸው፡ደም፣ውሃ፣ወተትና፡መዓር፡ወጣ።ጌታችንም፡አድኗቸው፡በስምህ፡የተማፀነውን፡መልካም፡ነገር፡አደርግታለሁ፡ብሎ፡ቃል፡ኪዳን፡ገባላቸው።በግብፅ፡አንስጣስዮስ፡ቴዎዶስዮስ፡ተብለው፡ሲነግሱ፡መላእክት፡የአባቱ፡የዳዊት፡መንግሥት፡ቅባት፡ቀቧቸው፤የመንግሥት፡ልብስ፡አለበሷቸው፤የመንግሥት፡ሥርዓትን፡ሁሉ፡ሰጧቸው።የጣዖታትን፡ቤት፡አፍርሱ፡ቤተ፡ክርስቲያንን፡ሥሩ፡በማለት፡ሕዳር12፡አዋጅ፡ነጋሪን፡ላኩ።ጌታችን፡በግብፅ፡ተሶዶ፡ሳለ፡ለአረጋዊ፡ቅዱስ፡ዮሴፍ፡የተናገረው፡ትንቢት፡ተፈፀመ”ከልጅህ፡የሚወለድ፡በግብፅ፡ያሉትን፡ጣዖቶች፡አፍርሶ፡ሐይማኖትን፡ያጸናል”፡ብሎ፡ነበር።እዲሁም፡ቅድስት፡አርሴማ፡ሳትወለድ፡በስሟ፡የተሰየመውን፡ታቦት፡በግብፅ፡ያገኙና፡ያከበሩ፡ናቸው(ገድለ፡አርሴማ፡7ኛ፡ተዓምር)።

በግብፅ፡ደብረ፡ምጥማቅ፡ማርያም፡በመጀመሪያ፡ሰርተው፡የቀደሱት፡አቡነ፡ሙሴ፡ናቸው።በተጨማሪ፡ብዙ፡የህንጻ፡ቤተ፡ክረስቲያንና፡የዋሻ፡ቤተ፡ክረስቲያን፡አንጸዋል።እንደ፡ቅዱሳን፡ብዙ፡ድንቅ፡ተዓምር፡አድርገዋል።ለምሳሌ፡አውሬ፡ገድሏቸው፡ተጠራቅሞ፡የነበረ፡አፅም፡ላይ፡ጸልየው፡አራት፡ሺህ፡የሞቱ፡ሰዎችን፡ከሞት፡አስነስዋል።40ዓመት፡በንግሥና፡ከቆዩ፡በኋላ፡ከብዙ፡ተከታዮቻቸው፡ጋር፡ወደ፡አስቄጥስ፡ገዳም፡ለምነና፡ስጓዙ፡በበረሃው፡ተርበው፡ለወደቁት ወደ፡እግዚአብሔር፡ሲጸልዩ፡መና፡ወርዶላቸው፡መግበዋል፡አስቄጥስ፡ገዳም፡ሲደርሶ፡አቡነ፡መቃርስ፡ነበሩ፡የተቀበሏቸው፡፡አቡነ፡ሙሴ፡በአስቄጥስ፡በአቡነ፡እንጦንስ፡ስም፡የመጀመርያውን፡ቤተ፡ክርስቲያን፡ሰርተው፡ከፈፀሙ፡በኋላ፡አቡነ፡እንጦንስንና፡አቡነ፡መቃርስ፡በምንኵስና፡ልብስ፣በመላእክት፡አስኬማ፣በቅንዓት፣በቀሚስና፡በቆብዕ፡ላይ፡ለ40ቀን፡ጸልየው፡ጥር22፡ተክለማርያም፡ብለው፡ሰይመው፡አመነኮሷቸው።በዚያውም፡አቡነ፡መቃርስ፡ከበታቻቸው፡ብፁዓዊ፡ሙሴን፡ሾሙ።በአስቄጥስ፡ብዙ፡ተከታዮቻቸውን፡አመንኵሰው፡ቀድሞ፡ወደ፡ሰሯቸው፡ቤተ፡መቅደሶች፡ይልኳቸው፡ነበር።የቀሩት፡ደግሞ፡በኋላ፡ወደ፡ኢትዮጵያ፡ሲመጡ፡አብረዋቸው፡መጥተዋል።
የኢትዮጵያ፡የመጀመርያው፡ጳጳስ፡አቡነ፡ሰላማ፡በማረፋቸው፡ሁለቱ፡ቅዱሳን፡ነገሥታት፡አብርሃ፡ወአጽብሃ፡ጳጳስ፡እንዲልኩላቸው፡ከእጅ፡መንሻ፡ጋር፡ወደ፡ግብፅ፡ላኩ።አቡነ፡አትናቴዎስ፡ፈቃደ፡እግዚአብሔር፡ጠይቀው፡አቡነ፡ሙሴ፡ከአስቄጥስ፡ገዳም፡ለኢትዮጵያውያን፡አባት፡እዲሆኑ፡አቡነ፡ሚናስ፡ብለው፡ሾሙ።ከሶስት፡ሺህ፡ልጆቻቸው፡ጋር፡ሆነው፡ብዙ፡ቅርስ፡ይዘው፡አባታችን፡ወደ፡ኢትዮጵያ፡ሲመጡ፡ህዝቡ፡በደስታ፡ተቀበሏቸው።ብዙ፡መጽሐፍትን፡ከአረብኛ፡ወደ፡ግእዝ፡ቋንቋ፡ተርጉመው፡ጽፈዋል።ይጽፉበት፡የነበረው፡ብዕር፡አድሮ፡በማግስቱ፡ለምልሞ፡አብቦ፡ይገኛል።ቀለም፡ይበጠብጡበት፡የነበረው፡የቀንድ፡ዋንጫም፡ከመሬት፡ተጣብቆ፡ያገኙት፡ነበር።በእጃቸው፡ሲያላቅቁት፡ከመሬት፡ጠበል፡ይፈልቃል፣በጠበሉም፡ህሙማንን፡ፈውሰውበታል።

በኢትዮጵያ፡አምስት፡መቶ፡የዋሻ፡ቤተ፡ክስቲያን፡ያነጹ፡ሲሆን፡በአጠቃላይ፡በመላው፡ዓለም፡ከዐሥር፡ሺህ፡በላይ፡ቤተ፡ክርስቲያ፡ሰርተዋል፣አንጸዋል(መለከት፡መጽሔት፡2007ዓ.ም)።በእንቁና፡በእብነ፡በረድ፡ከሰራቸው፡ቤተ፡ክረስቲያኖች፡መካከል፡በአራራት፡ደብር(ከምድር፡ጥፋት፡በኋላ፡የኖኅ፡መርከብ፡መጀመርያ፡ያረፈችበት)በጻድቁ፡ኖኅ፡ስም፣አብርሃም፡ሥላሴን፡በድንኳኑ፡ባስተናገደበት፡ስፍራ፡በቅድስት፡ሥላሴ፡ስም፣በሕንድ(በሐዋርያው፡ቅዱስ፡ቶማስ፡መቃብር፡ቦታ)በቅዱስ፡ቶማስ፡ስም፣በአርማንያና፡በግርስ(በሰማዕቱ፡ቅዱስ፡ጊዮርጊስ፡ስጋውን፡ባሳረፉበት፡ቦታ)በቅዱስ፡ጊዮርጊስ፡ስም።

*በኢትዮጵያ፡በአቡነ፡ሙሴ፡ከታነጹት፡ቤተ፡ከርስቲያ፡ውስጥ፡የተወሰኑት፦
1.የድባ፡መቅደሰ፡ማርያም፡አቡነ፡ሙሴ፡አንድነት፡ገዳም(ባለ፡ሰባት፡መቅደስ፡ፎቅ)፣የረፍታቸው፡ቦታ፣በትረ፡ሙሴያቸውና፡የእጅ፡መስቀላቸው፡ያለበት(ሰሜን፡ወሎ፡ዳውንት)
2.ደብረ፡ከርቤ፡ግሸን፡ማርያም፡ላይ፡በምስራቅ፡በኩል፡ስውር፡ቤተ፡መቅደስ(ድርሳነ፡ራጉኤል)
3.አእማድ፡ቅድስት፡ሥላሴ፡ገዳም(መቄት)እንደ፡አቡነ፡አሮን፡መንክራዊ፡ጣራው፡ክፍት፡ሆኖ፡ዝናብ፡የማይገባው፣
በመጨረሻ፡ብጹዕ፡አቡነ፡ሙሴ፡በቤተ፡ሚናስ፡ቤተመቅደስ፡የድባ፡መቅደሰ፡ማርያም፡አቡነ፡ሙሴ፡ገዳም፡መሰከረም4፡በዕለተ፡እሁድ፡አረፋ።ወርሃዊ፡በዓላቸው፡ወር፡በገባ፡በ4፡ነው።በተለይ፡ጋብቻን፡የሚቀድሱ፣ክህነት፡የሚባርኩ፣መናንያንን፡የሚያጸኑ፡አረጋዊን፡አባት፡ናቸው።ምንጭ፡የድባ፡መቅደሰ፡ማርያም፡አቡነ፡ሙሴ፡አንድነት፡ያሳተመው፡መጽሔት።
*የዕለቱ፡ምስባክ፦”ወወሀብኮሙ፡ትእምርተ፡ለእለ፡ይፈርሁከ።ከመ፡ያምሥጡ፡እምገጸ፡ቅስት።ወይድኀኑ፡ፍቁራኒከ”።መዝ59፥9-10።የሚነበበው፡ወንጌል፡ዮሐ6፥1-22።የሚቀደሰው፡ቅዳሴ፡የሠለስቱ፡ምዕት፡ቅዳሴ፡ነው።መልካም፡በዓል፡ለሁላችንም፡ይሁንልን።